ስምዖን/የበላኤ ሰብእ ታሪክ በተአምረ ማርያም ከተመዘገቡትና
የእመቤታችንን አማላጅነት ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱ ነው፡፡ ዘወትር በየዓመቱ በየካቲት 16 ቀን ይዘከራል፣
ይተረካል፣ ይተረጎማል፡፡ የስምዖን በላኤ ሰብእ ዘመን በሁለት ይከፈላል፡-
ደገኛው የስምዖን/በላኤ ሰብእ ዘመን
በላኤ ሰብእ አስቀድሞ አብርሃማዊ ኑሮ የሚኖር ደገኛ ሰው
ነበር፡፡ እንግዳ በመቀበል ዘመኑን የፈጀ ባዕለ ጸጋ ነው፡፡ ነገር ግን የሰውን ልጆች ጽድቅ የማይወደው ዲያብሎስ
ሴራ አሴራበት፡፡ በቅድስት ሥላሴ አምሳል እንግዳ ሆኖ ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በላኤ ሰብእም እንደ አብርሃም ዘመን ቅድስት
ሥላሴ ከቤቱ በመገኘታቸው ተደስቶ ምንጣፍ ጎዝጉዞ ወገቡን ታጥቆ አስተናገደው፡፡ አብርሃም ለሥላሴ ከቤቱ ከብት
መርጦ መሥዋዕት እንዳቀረበ በላኤ ሰብእም የሰባውን ፍሪዳ አቀረበ፡፡ ዲያብሎስ ግን የምትወደኝ ከሆነ ልጅህን
እረድልኝ ሲል ጠየቀው፡፡
በላኤ ሰብእ የዋሕና ደግ ክርስቲያናዊ ስለ ነበር እሺ በጄ ብሎ
ልጁን አቅርቦ ሰዋው፡፡ በኋላም “አስቀድመህ ቅመሰው” የሚል ትእዛዝ ሰጠው፡፡ በላኤ ሰብእም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡
ዲያብሎስም ተሰወረው፡፡ በላኤ ሰብእ የልጁን ሥጋ በመብላቱ ደሙንም በመጠጣቱ እንዲሁም በዚህ ጊዜ ሥላሴ ነው ብሎ
በቤቱ የተቀበለው ዲያብሎስ ምትሐቱን ጨርሶ በመሰወሩ የተፈጠረበት ድንጋጤ ጠባዩ እንዲለወጥ አእምሮው እንዲሰወር
አድርጎታል፡፡ ዲያብሎስ ልቡናውን ስለሰወረበት ከዚያ በኋላ ያገኘውን ሰው ሁሉ የሚበላ ሆኗል፡፡
አሰቃቂው የስምዖን/በላኤ ሰብእ ዘመን
በላኤ ሰብእ አእምሮውን ካጣ በኋላ አስቀድሞ ቤተሰቦቹን በላ፤
ከዚያ በኋላ የውኃ መጠጫውንና ጦሩን ይዞ ከሀገሩ ወጣ፡፡ በየቦታው እየዞረ በጉልበቱ ተንበርክኮ፤ በጦሩ ተርክኮ
ያገኘውን ሁሉ ይበላ ጀመር፡፡ ይኸ ጊዜ በላኤ ሰብእ ፍጹም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የዋለበት አሰቃቂው የበላኤ ሰብእ
ዘመን ነበር፡፡
የንስሐ ዘመኑ
ያገኘውን ሁሉ እየገደለ የገደለውንም እየበላ ሲዘዋወር ከአንድ
መንደር ደረሰ፡፡ በዚያውም የሚበላውን ሲሻ ሰውነቱን በቁስል የተወረረ ሰው ተመለከተ፡፡ ይበላውም ዘንድ
ተንደረደረ፡፡ ያ ድኃ ፈጽሞ የተጠማ ነበርና ውኃ ይሰጠው ዘንድ በላኤ ሰብእን ለመነው፣ በእግዚአብሔር ስም፣
በጻድቃን በሰማእታት ሁሉ ለምኖት ሊራራለት አልቻለም፡፡ በመጨረሻም “ስለ እመቤታችን ብለህ” ሲለው ይህቺ ደግ
እንደሆነች በልመናዋም ከሲዖል የምታድን እንደሆነች እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሮ ሰምቼ ነበር አለው፡፡ በላኤ ሰብእ “ወደ
ልቡናው ተመለሰ”፡፡ ጨካኝ የነበረው ልቡ ራርቶ ለድኃው ጥርኝ ውኃ ሰጠው፡፡ በሕይወቱም ከባድ ውሳኔ ወሰነ፡፡
ከእንግዲህ ከዋሻ ገብቼ ስለ ኀጢአቴ ማልቀስ ይገባኛል፣ እህል ከምበላ ሞት ይሻለኛል” ብሎ እየተናገረ ንስሓ ገብቶ
እህልና ውኃ ሌላም አንዳችም ሳይቀምስ በእግዚአብሔር ኀይል ሃያ አንድ ቀን ከተቀመጠ በኋላ ይህ በላኤ ሰብእ ሞተ፡፡
ድኅነተ ስምዖን/በላኤ ሰብእ
ከዚህ በኋላ ተአምረ ማርያም የሚተርክልን የበላኤ ሰብእ መዳን
ነው፡፡ የበላኤ ሰብእ ነፍስ በፈጣሪ ፊት ለፍርድ ቆመች፡፡ የመጀመሪያው ፍርድም ተሰማ፤ “ይህቺን ነፍስ ወደ ሲዖል
ውሰዷት” የሚል፡፡ እመቤታችን ማርልኝ ስትል ለመነችው፡፡ በላኤ ሰብእ ያጠፋቸው ነፍሳትና የሰጠው ጥርኝ ውኃ በሚዛን
ተመዘነ በመጀመሪያም የበላኤ ሰብእ ጥፋት መዘነ፡፡ ነገር ግን እመቤታችን ቃል ኪዳኗ ባረፈበት ጊዜ ጥርኝ ውኃው
ሚዛን ደፋ፡፡ የበላኤ ሰብእ ነፍስ በእመቤታችን አማላጅነት ዳነች ይህም የእግዚአብሔር ቸርነት የሚያሳይ ነው፡፡
“እንበለ ምግባር ባህቱ እመ ኢየጸድቅ አነ ቦኑ ለከንቱ ኪዳንኪ ኮነ” በማለት የመልክአ ኪዳነ ምሕረት ደራሲ
የተናገረው አስቀድሞም በወንጌልም በደቀ መዝሙር ስም ብቻ ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ ዋጋው አይጠፋበትም /ማቴ.10፥42/
የሚለው ቃል ተፈጸመ፡፡
|