ስምዖን/የበላኤ ሰብእ ታሪክ በተአምረ ማርያም ከተመዘገቡትና
የእመቤታችንን አማላጅነት ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱ ነው፡፡ ዘወትር በየዓመቱ በየካቲት 16 ቀን ይዘከራል፣
ይተረካል፣ ይተረጎማል፡፡ የስምዖን በላኤ ሰብእ ዘመን በሁለት ይከፈላል፡-
ደገኛው የስምዖን/በላኤ ሰብእ ዘመን
በላኤ ሰብእ አስቀድሞ አብርሃማዊ ኑሮ የሚኖር ደገኛ ሰው
ነበር፡፡ እንግዳ በመቀበል ዘመኑን የፈጀ ባዕለ ጸጋ ነው፡፡ ነገር ግን የሰውን ልጆች ጽድቅ የማይወደው ዲያብሎስ
ሴራ አሴራበት፡፡ በቅድስት ሥላሴ አምሳል እንግዳ ሆኖ ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በላኤ ሰብእም እንደ አብርሃም ዘመን ቅድስት
ሥላሴ ከቤቱ በመገኘታቸው ተደስቶ ምንጣፍ ጎዝጉዞ ወገቡን ታጥቆ አስተናገደው፡፡ አብርሃም ለሥላሴ ከቤቱ ከብት
መርጦ መሥዋዕት እንዳቀረበ በላኤ ሰብእም የሰባውን ፍሪዳ አቀረበ፡፡ ዲያብሎስ ግን የምትወደኝ ከሆነ ልጅህን
እረድልኝ ሲል ጠየቀው፡፡
በላኤ ሰብእ የዋሕና ደግ ክርስቲያናዊ ስለ ነበር እሺ በጄ ብሎ
ልጁን አቅርቦ ሰዋው፡፡ በኋላም “አስቀድመህ ቅመሰው” የሚል ትእዛዝ ሰጠው፡፡ በላኤ ሰብእም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡
ዲያብሎስም ተሰወረው፡፡ በላኤ ሰብእ የልጁን ሥጋ በመብላቱ ደሙንም በመጠጣቱ እንዲሁም በዚህ ጊዜ ሥላሴ ነው ብሎ
በቤቱ የተቀበለው ዲያብሎስ ምትሐቱን ጨርሶ በመሰወሩ የተፈጠረበት ድንጋጤ ጠባዩ እንዲለወጥ አእምሮው እንዲሰወር
አድርጎታል፡፡ ዲያብሎስ ልቡናውን ስለሰወረበት ከዚያ በኋላ ያገኘውን ሰው ሁሉ የሚበላ ሆኗል፡፡
አሰቃቂው የስምዖን/በላኤ ሰብእ ዘመን
በላኤ ሰብእ አእምሮውን ካጣ በኋላ አስቀድሞ ቤተሰቦቹን በላ፤
ከዚያ በኋላ የውኃ መጠጫውንና ጦሩን ይዞ ከሀገሩ ወጣ፡፡ በየቦታው እየዞረ በጉልበቱ ተንበርክኮ፤ በጦሩ ተርክኮ
ያገኘውን ሁሉ ይበላ ጀመር፡፡ ይኸ ጊዜ በላኤ ሰብእ ፍጹም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የዋለበት አሰቃቂው የበላኤ ሰብእ
ዘመን ነበር፡፡
የንስሐ ዘመኑ
ያገኘውን ሁሉ እየገደለ የገደለውንም እየበላ ሲዘዋወር ከአንድ
መንደር ደረሰ፡፡ በዚያውም የሚበላውን ሲሻ ሰውነቱን በቁስል የተወረረ ሰው ተመለከተ፡፡ ይበላውም ዘንድ
ተንደረደረ፡፡ ያ ድኃ ፈጽሞ የተጠማ ነበርና ውኃ ይሰጠው ዘንድ በላኤ ሰብእን ለመነው፣ በእግዚአብሔር ስም፣
በጻድቃን በሰማእታት ሁሉ ለምኖት ሊራራለት አልቻለም፡፡ በመጨረሻም “ስለ እመቤታችን ብለህ” ሲለው ይህቺ ደግ
እንደሆነች በልመናዋም ከሲዖል የምታድን እንደሆነች እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሮ ሰምቼ ነበር አለው፡፡ በላኤ ሰብእ “ወደ
ልቡናው ተመለሰ”፡፡ ጨካኝ የነበረው ልቡ ራርቶ ለድኃው ጥርኝ ውኃ ሰጠው፡፡ በሕይወቱም ከባድ ውሳኔ ወሰነ፡፡
ከእንግዲህ ከዋሻ ገብቼ ስለ ኀጢአቴ ማልቀስ ይገባኛል፣ እህል ከምበላ ሞት ይሻለኛል” ብሎ እየተናገረ ንስሓ ገብቶ
እህልና ውኃ ሌላም አንዳችም ሳይቀምስ በእግዚአብሔር ኀይል ሃያ አንድ ቀን ከተቀመጠ በኋላ ይህ በላኤ ሰብእ ሞተ፡፡
ድኅነተ ስምዖን/በላኤ ሰብእ
ከዚህ በኋላ ተአምረ ማርያም የሚተርክልን የበላኤ ሰብእ መዳን
ነው፡፡ የበላኤ ሰብእ ነፍስ በፈጣሪ ፊት ለፍርድ ቆመች፡፡ የመጀመሪያው ፍርድም ተሰማ፤ “ይህቺን ነፍስ ወደ ሲዖል
ውሰዷት” የሚል፡፡ እመቤታችን ማርልኝ ስትል ለመነችው፡፡ በላኤ ሰብእ ያጠፋቸው ነፍሳትና የሰጠው ጥርኝ ውኃ በሚዛን
ተመዘነ በመጀመሪያም የበላኤ ሰብእ ጥፋት መዘነ፡፡ ነገር ግን እመቤታችን ቃል ኪዳኗ ባረፈበት ጊዜ ጥርኝ ውኃው
ሚዛን ደፋ፡፡ የበላኤ ሰብእ ነፍስ በእመቤታችን አማላጅነት ዳነች ይህም የእግዚአብሔር ቸርነት የሚያሳይ ነው፡፡
“እንበለ ምግባር ባህቱ እመ ኢየጸድቅ አነ ቦኑ ለከንቱ ኪዳንኪ ኮነ” በማለት የመልክአ ኪዳነ ምሕረት ደራሲ
የተናገረው አስቀድሞም በወንጌልም በደቀ መዝሙር ስም ብቻ ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ ዋጋው አይጠፋበትም /ማቴ.10፥42/
የሚለው ቃል ተፈጸመ፡፡
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛውን
ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ አስመራጭ ኮሚቴ በመሠየም
እጩ ፓትርያርኮችን ለመምረጥ ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከካህናት፤ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች፤ ከማኅበረ ቅዱሳን፤
እንዲሁም ከምእመናን ጥቆማ እንዲያካሒዱ ተደርጓል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ጥቆማውን በግብአትነት በመጠቀም አምስት ሊቃነ
ጳጳሳትን በእጩነት በማቅረብ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅርቧል፡፡ የቅዱስ
ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ከየካቲት 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ውይይት በማካሔድ አምስቱም ሊቃነ ጳጳሳት
በእጩነት እንዲቀርቡ አጽድቋል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚካሔደው የስድስተኛው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የፓትርያርክ ምርጫ የቀረቡት ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ ማትያስ
በኢየሩሳሌም የኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር
ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የምዕራብና
የደቡብ አዲስ አበባና የከፋ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ ብፁዕ አቡነ
ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አጭር የሕይወት ታሪካቸውን
እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-
ብፁዕ አቡነ ማትያስ :-
የቀድሞው የአባ ተክለ ማርያም ዐሥራት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ
ማትያስ በ1934 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ቅዳሴ፣ ዜማ፣ ቅኔ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ ተምረዋል፡፡
በ1948 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዲቁናን ጮኸ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ ከመ/ር ዐሥራተ ጽዮን ኰኲሐ ሃይማኖት መዓርገ ምንኩስናን ተቀብለዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ መዓርገ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡
በጮኸ ገዳም በቄሰ ገበዝነት፣ በመጋቢነትና በልዩ ልዩ ገዳማዊ
ሥራ አገልግለዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ሐዲስ ኪዳንን አስተምረዋል፡፡ ከ1964 -- 68 ዓ.ም
በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት
ዓመታት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ጥር 13
ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በኢየሩሳሌም
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ :-
የቀድሞው አባ ኅሩይ ወልደ ሰንበት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ጸዋትዎ ዜማ፣ ቅኔ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ባሕረ ሐሳብና ሐዲስ ኪዳንን ተምረዋል፡፡ በ1945 ዓ.ም
ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዲቁና፤ በ1964 ዓ.ም ምንኩስናን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም
ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቅስና በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሰላማ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ጽጌ ገዳም
በመዘምርነትና በቅዳሴ አገልግለዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ
እድ የከፋ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ
ጳጳስ ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ :-
ነሐሴ 16 ቀን 1944 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ክፍለ ሀገር በሸኖ አውራጃ ልዩ ስሙ ጨቴ ጊዮርጊስ በተባለው ቦታ ተወለዱ፡፡ የቀድሞ ስማቸው
ቆሞስ አባ ኀይለጊዮርጊስ ኀይለ ሚካኤል ይባላል፡፡ ፊደል የቆጠሩት፣ ዜማን የተማሩት፣ ቅኔን የተቀኙት በሀፋፍ
ማርያም በኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ ገዳም ነው፡፡ ቅዳሴን በዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት
ተምረዋል፡፡ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት ለ4 ዓመታት ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀው ዘመናዊ
ትምህርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል በማጠናቀቅ በምዕራብ ጀርመን እሸት ኬርከሌ መንፈሳዊ ት/ቤት ስለ ገዳማት
አስተዳዳር አጥንተዋል፡፡
ሐምሌ 5 ቀን 1991 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት የባሌ
ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
ምንጭ፡- ዜና ቤተ ክርስቲያን 31ኛ የዓመት ቁ.3፣ ጥር 4 ቀን 1971 32ኛ ዓ.ም ቁ.4
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡-
የቀድሞ
ስማቸው መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ይባላል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 1946 ዓ.ም በደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት
ልዩ ስሙ ደብረ ብርሃን ለንጓጥ ሥላሴ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ግራ ጌታ መኮንን ኀይሉ እናታቸው ወ/ሮ አታላይ ደርሰህ
ይባላል፡፡ ዜማ፣ አቋቋም፣ ቅኔ፣ ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተምረዋል፤ የቅኔ መንገድ ከነአገባቡ ተምረው በመምህርነት
ተመርቀዋል በ1956 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ዲቁና ተቀብለዋል፡፡
ጳጉሜን 3 ቀን 1981 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሥርዓተ
ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ ኅዳር 12 ቅን 1982 ዓ.ም የቅስና ማዕረግ ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ
መዓርገ ቁምስና ተቀብለዋል፡፡ ከ1982 – 87 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ
በጽርሐ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከሠኔ 20 ቀን
1987-1990 ዓ.ም በምሥራቅ ሐረርጌ ሐደሬ ጤቆ መካነ ሥላሴ ደብር፣
ከየካቲት 1990-93 ዓ.ም የድሬዳዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ
ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከሠኔ 1 ቀን 1993 ዓ.ም - ሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ ለጵጵስና መአርግ እስከ
በቁበት ዘመን በአዲስ አበባ ቦሌ ደብረ ምጽላል እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን
1994 ዓ.ም የሰሜን ወሎ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 1997
ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው
ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ ፤ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፡-
በ1955 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ልዩ ስሙ ምንታምር ቀበሌ ከአቶ ጌታነህ የኋላሸትና ከወ/ሮ አምሳለ ወርቅ ማሞ ተወለዱ፡፡
አቋቋም፣ ቅኔ ከነአገባቡ ቅዳሴ ኪዳን አንድምታ፣ ዜማ፣ ሠለስት፣ አርያም፣ ጾመ ድጓ፣ ቁም ዜማ ተምረዋል፡፡
በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ዲቁና ተቀብለው ቅስና ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀብለዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም
በደብረ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ
መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለ4 ዓመታት ያህል ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በሆላንድ ሆህ እስኩል የነገረ መለኮት
ትምህርት ቤት ገብተው ለ4 ዓመታት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በሰበካ ጉባኤ አደራጅነት፣ በሰ/ት
ቤት ሓላፊነት፣ አ/አ ሀገረ ስብከት ሸሮ ሜዳ መንበረ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሰባኪነት፣ በአ/አ ሀገረ ስብከት
በአቃቂ መድኀኔዓለም፣ በቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል፣ በሳሎ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በመካነ ሰማዕት
ቅዱስ ቂርቆስ ደብርና በሐረር ደብረ ገነት መድኀኔዓለም አብያተ ክርስቲያናት በአስሪተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡
በውጭ ሀገር በአሜሪካ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል በአውሮፓ ስዊዘርላንድ በጀኔቫ፣ በሎዛን፣ በዙሪክና በበርንባዝል ከተሞች
ባሉ አድባራት በቀዳሽነትና በሰባኪነት አገልግለዋል፡፡
ነሐሌ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የዋግ ህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የየወላይታና
ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
‹አራቱ ኃያላን› በጎንደር
‹አራቱ ኃያላን› መጽሐፍን የተመለከተ ልዩ መርሐ ግብር ጎንደር ላይ ለማዘጋጀት ከታቀደ ቆየ፡፡ በአዲስ አበባ እንዲመረቅ ከታቀደበት ጊዜ ጋር አብሮ ነበር መርሐ ግብሩ የተያዘው፡፡ በአንድ በኩል ጎንደር ታሪካዊት ከተማ በመሆኗ፤ በሌላም በኩል የሊቃውንቱ መፍለቂያ፣ የሀገሪቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕውቀት ማዕከል (Center of Excellence) በመሆኗ፣ ከዚያም አልፎ ደግሞ ከዚህ በፊት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ራእየ ዮሐንስን በተመለከተ በድሬዳዋ አድርገን ነበርና ዕድሉን ለሰሜኑ ለመስጠት፣ በመጨረሻም ከደሴ እስከ ደብረ ማርቆስ ላሉት ማዕከል ናትና ለአካባቢው ነዋሪዎችም አማራጭ ለመስጠት የታሰበ ነበር፡፡
ከመጀመሪያው ጀምሮ ሦስት አካላት ለመርሐ ግብሩ መሳካት ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአግዮስ ዋናው ቢሮ፤ በጎንደር ከተማ የሚገኙት የጎንደር ከተማ ወጣቶች ጥምረትና ሁለቱ የዝግጅት ኮሚቴው መሪዎች (ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑና ዲያቆን ኢንጂነር መላኩ እዘዘው)፡፡
አስቀድሞ መርሐ ግብሩ የተያዘው በታየ በላይ ሆቴል ነበር፡፡ ይህንን መሰል መርሐ ግብር በከተማዋ ማካሄድ የተለመደ ባለመሆኑ ለመጥራት የታሰበው ከአራት መቶ የማይበልጡ እንግዶችን ነበር፡፡ በኋላ ግን የከተማዋም ሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ፍላጎት እየጨመረ መጣ፡፡ መርሐ ግብሩንም በሌላ ቦታ ማከናወን የግድ ሆነ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ አስቀድሞ አዳራሹን በአነስተኛ ዋጋ በመስጠት፣ በኋላም ቦታው ሲቀየር ያስያዝነውን ገንዘብ በመመለስ የታየ በላይ ሆቴል ያደረገውን ትብብር እዚህ ላይ አመስግነን እናልፋለን፡፡
ለሰፊው መርሐ ግብር የተመረጠው ቦታ በጣልያን ዘመን የተሠራውና በጎንደር ከተማ እምብርት የሚገኘው የጎንደር ሲኒማ ቤት ነው፡፡ ሲኒማ ቤቱን የሚፈቅደው የከተማዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በመሆኑ ዲያቆን ሙሉቀን የከተማውን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባልደረባን አናገራቸው፡፡ እርሳቸውም ፈቃደኛ ሆነው አዳራሹን እንድንከራይ ደብዳቤውን ወደሚመለከተው አካል መሩት፡፡ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው አቶ ጌታሁንም ለዚህ መርሐ ግብር አዳራሽ መከራየት የለባችሁም ብለው በነጻ ፈቀዱልን፡፡ የከተማው ከንቲባም መርሐ ግብሩን በደስታ ተቀበሉት፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጡ፡፡
የከተማው ሲኒማ ቤት ታኅሣሥ 20 ቀን ምንም መርሐ ግብር እንዳልያዘ ተረጋገጠ፡፡ ለሌሎች በኪራይ ይሰጥ የነበረው አዳራሽም በነጻ ተፈቀደ፡፡ ማስታወቂያውም ተቀይሮ ወደ ጎንደር ሲኒማ ቤት ተዛወረ፡፡ የታተመው የመግቢያ ካርድ 800 ያህል ነበር፡፡ ከጎንደር ዙሪያ ከተሞች፣ ከባሕርዳር፣ ከደብረ ታቦር፣ ከደብረ ማርቆስ፣ ከሞጣ፣ ከወልድያና ከሌሎችም ከተሞች መርሐ ግብሩን ለመሳተፍ የሚጠይቁ ሰዎች በመብዛታቸው ስማቸውን በስልክ መመዝገብ ተጀመረ፡፡
ፋና ሬዲዮ ዋናው ጣቢያ፣ ፋና ሬዲዮ የጎንደር ጣቢያና የባሕርዳር ኤፍ ኤም ሬዲዮኖች መርሐ ግብሩን የተመለከቱ ማስታወቂያዎችንና ፕሮግራሞችን መሥራታቸው ከጎንደር ከተማ ወጣ ባካሉ ከተሞች የሚገኙ ተሳታፊዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርገውታል፡፡
የከተማው የሥራ ኃላፊዎች፣ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሥራ አስኪያጅና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ የጎንደር ወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማው አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በኣታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ቤት መምህርና የምስክር ተማሪዎች፣ የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የሐዲሳት ትርጓሜ ትምህርት ቤት መምህርና የምስክር ተማሪዎች፣ የአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል የቅኔ ጉባኤ ቤት መምህርና የምስክር ተማሪዎች፣ የሠለስቱ ምእት የመጽሐፈ መነኮሳት ትርጓሜ መምህርና የምስክር ተማሪዎች፣ የደብረ መድኃኒት ዐቢየ እግዚእ የብሉያት ምስክር ትምህርት ቤት መምህርና የምስክር ተማሪዎች፣ የመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባኤያት የምስክር ተማሪዎች፣ በደብረ ብርሃን ሥላሴ የገለዓድ የቅኔ ትምህርት ቤት መምህርና የምስክር ተማሪዎች፣ የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም የአቋቋም መምህርና የምስክር ተማሪዎችና ሌሎችም ታላላቅ ሊቃውንት ተጋብዘዋል፡፡
በጎንደር ከተማ ከ4000 በላይ የአብነት ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ እየመገበ የሚያስተምረው ደጉ የጎንደር ከተማ ሕዝብ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ለመጥራት ብንፈልግ እንኳን ሁሉንም የሚይዝ አዳራሽ ግን በከተማዋ ውስጥ የለም፡፡ በዚህም ምክንያት ልንጋብዝ የቻልነው አስመስካሪዎችን (የዶክትሬት ተማሪዎችን) ብቻ ነው፡፡
መርሐ ግብሩን ለመሳተፍ ከዱባይ፣ ከአውስትራልያ፤ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ እንግዶች ወደ ጎንደር ተጉዘው ነበር፡፡ ታኅሣሥ 19 ቀን በጎንደር ልደታ ቤተ ክርስቲያን የአኮቴት መንፈሳዊ የሌቴቭዥን መርሐ ግብር የልደት በዓል ዝግጅት ቀረጻ ስለነበረው ሁለቱንም መርሐ ግብሮች በካሜራ ለማስቀረት የወንድ ወሰን ዲጂታል ስቱዲዮ ባለቤት አቶ ወንድ ወሰን ከአዲስ አበባ፣ ወንድማችን ደረጀ ደግሞ ከዱባይ በሥፍራው ለቀረጻ ተገኝተው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከአዲስ አበባ ሃያ ልዑካን በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡
እሑድ ታኅሣሥ 20 ቀን ከቀኑ ሰባት ሰዓት አዳራሹ ሲከፈት የከተማው ሕዝብ እንደ ንብ ነበር የተመመው፡፡ የጎንደር ከተማ ወጣት ማኅበራት ጥምረት አባላት አዳራሹን በማስተካከል፣ ባነሮቹን በመለጠፍ፣ እንግዶቹን በማስተናገድ፣ ካርድ የያዙትን ካልያዙት በመለየት፣ ሊቃውንቱንና ሽማግሌዎችን፣ እናቶችንና እንግዶችን ቅድሚያ በመስጠት ባይተባበሩ ኖሮ ያንን ሁሉ ሕዝብ ማስተናገድ ከባድ በሆነ ነበር፡፡ አዳራሹ የሞላው በተከፈተ በ30 ደቂቃ ውስጥ ነው፡፡ የጥምረቱ ወጣቶች የሲኒማ ቤቱ ላይኛውን ክፍል በማስከፈት የመጥሪያ ካርድ ያልያዙት ተሳታፊዎች ወደ ፎቅ እንዲገቡ አደረጉ፡፡ አዳራሹ ወንበር በያዙ፣ መሬት ላይ በተቀመጡና ቆመው በሚከታተሉ ታዳሚዎች ተሞላ፡፡
መርሐ ግብሩ የተጀመረው በብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎት ሲሆን ቀጥሎም ዲያቆን ምንዳየ ብርሃኑ መዝሙር አቀረበ፡፡ ከዚያም የመጽሐፉን አዘገጃጀት በተመለከተ ገለጻ ተደረገ፡፡ ከገለጻው በኋላ ሦስቱ ምሁራን ወደ መድረክ እንዲመጡ በአወያዩ በዐሥራት ከበደ ጥሪ ቀረበ፡፡
ዶክተር ውዱ ጣፈጠ፣ ዶክተር አምሳሉ ተፈራና ሠርጸ ፍሬ ስብሐት ወደ መድረክ ወጡ፡፡ የመጀመሪያውን ዕድል ያገኙት ዶክተር ውዱ ጣፈጠ መጽሐፉ ከታሪክ አንጻር ያለውን ፋይዳ ተነተኑ፤ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ደግሞ ለመንፈሳውያን መሪዎች የሚኖረውን ፋይዳ አመለከቱ፣ ሠርጸ ፍሬ ስብሐትም ቅርስንና ታሪክን ከመዘገብ አንጻር ያለውን ፋይዳ ገለጸ፡፡
ከገለጻው በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆነ፡፡ ከሊቃውንት፣ ከምሁራንና ከከተማው ነዋሪዎች አያሌ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ተነሡ፡፡ ከመጽሐፉ አልፈው ታሪክንና ቅርስን፣ ባህልንና ማንነትን፣ የትምህርት ተቋማትንና የተተኪውን ትውልድ ድርሻ፣ የቤተ ክህነትንና የሊቃውንቱን ኃላፊነት የተመለከቱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡ የመድረኩ አቅራቢዎችም ያላቸውን ሃሳብ አካፍለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ የጎንደር ከተማ ባህል ቱሪዝም መምሪያና የጎንደር ማዕከል ለመጽሐፉ አዘጋጅ ያዘጋጁትን ስጦታ በብጽዕ አቡነ ኤልሳዕ በኩል አበርክተዋል፡፡ መርሐ ግብሩም በብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ ጸሎት ተዘግቷል፡፡
ከአዳራሹ መርሐ ግብር በመቀጠል ጉዞ የተደረገው የከተማው ከንቲባ ለልዑካን ቡድኑ ወዳዘጋጁት እራት ነበር፡፡ የጎንደርን ከተማ መርሐ ግብር ልዩ ከሚያደርጉት አንዱ የከተማው ከንቲባና የከተማው ባህል ቱሪዝም መምሪያ በንቃት የተሳተፉበት፣ ቢሮክራሲ ሳያበዙ ጉዳዩን ጉዳያችን ብለው የሠሩበት፣ በመርሐ ግብሩም ላይ በንቃት የተሳተፉበት፣ በመጨረሻም ለልዑካኑ የእራት ግብዣ ያደረጉበት መሆኑ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ድጋፍ ከመርሐ ግብሩ መወጠን ጀምሮ እስከ ፍጻሜው የዘለቀ ነበር፡፡
ለዚህ መርሐ ግብር መሳካት የከተማው ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረና የባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው አቶ ጌታሁን ሥዩም ያደረጉት አስተዋጽዖ በጉባኤው በተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉ ያስመሰገናቸው፣ ከሌሎች ቦታዎች በመጡት እንግዶችም ያስደነቃቸው ነበር፡፡ ከእነርሱም በተጨማሪ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ የጎንደር ከተማ ወጣት ማኅበራት ጥምረት ይህ ቀረሽ የማይባል ሥራ ሠርተዋልና ይመሰገናሉ፡፡
እንግዶቹ ያረፉበት የጃን ተከል ሆቴል ባለቤት አቶ ተመስገን አምስት ክፍሎችን በነጻ በመስጠት፣ ለሌሎች ደግሞ ቅናሽ በማድረግ ለመርሐ ግብሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽ አድርገዋል፡፡ አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ወንድማችን ለመርሐ ግብሩ የተዘጋጀውን ውኃ በራ ወጭ ያቀረበ ሲሆን፣ ዳሽን ቢራ ደግሞ ሌሎች ወጭዎችን በመሸፈን አጋርነቱን አሳይቷል፡፡
ይህ መርሐ ግብር እንዲሳካ ቀን ከሌት የጣረው ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑን ሁሉም ሰው እድሜ ከጤና ያድልህ ብሎታል፡፡ አብሮት ነገሮችን ሁሉ ሲያመቻች የቆየውን መልአኩ እዘዘውንም እንዲሁ፡፡
የጎንደር መርሐ ግብር በክልል ከተሞች ጠንክረን መሥራት እንዳለብን የተማርንበት፤ ከኳስና ከዘፈን፣ ከጫትና ከጌም ውጭ ቁም ነገር ትቷል ብለን የምንወቅሰው ወጣት ለቁም ነገር ያለው ትጋት ያየንበት፤ ቀና የሆኑና ለሥራ የተነሡ የመስተዳደር አካላት ከተገኙ ሕዝብና መንግሥት ተቀራርበው በመሥራት የተግባቦት ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ የታየበት፣ ‹እኛ ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፣ የሰማዩም አምላክ ያከናውንልናል› የተባለውን ቃል በተግባር ያየንበት መርሐ ግብር ነበረ፡፡
የጎንደር ከተማ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነቱና ደግነቱ ገና ያልጠፋበት፣ ለታሪኩና ለባሕሉ የሚቆረቆር፣ ሳይሰቀቅ ከየሀገሩ የሚመጡ ተማሪዎችን አብልቶ አሳድሮ የሚያስተምር፣ ባወቁት ቁጥር ይበልጥ የሚናፈቅ ሕዝብ መሆኑን አይተናል፡፡ ያኑርልን፡፡
ስለአብነት ትምህርት ቤቶች የሚያስረዳው “በእንተ ስማ ለማርያም” የተሰኘው ዐውደ ርዕይ በሲያትል ለሕዝብ እይታ ቀረበ |
በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል “በእንተ ስማ ለማርያም” (ስለ እመቤታችን ማርያም ! ) በሚል መሪ ቃል ያሰናዳው በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ላይ ያተኮረው ብዙኃን የቤተክርስቲያን ልጆች የተሳተፉበት ዐውደ ርዕይ በሲያትል ንዑስ ማዕከል አዘጋጅነት መጋቢት 7 እና መጋቢት 8 2005 ዓ/ም በሲያትል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ለሕዝብ እይታ ቀርቧል::
ዐውደ ርዕዩ ቅዳሜ መጋቢት 7 2005 ዓ/ም በሲያትልና በአቅራቢያው ካሉ ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ የሰባካ ጉባኤ አባላት፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ደመቅ ባለ ሥነ ሥርዓት ተከፍቷል::
በዚሁ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል መልእክት በዲ/ ተገኔ ተክሉ የቀረበ ሲሆን በመክፈቻው ላይ በተገኙ ካህናትና ተጋባዥ እንግዶች የተለያየ አስተያየት ተሰጥቷል።
ለሁለት ቀን ክፍት ሆኖ የቆየውን ዐውደ ርዕይ ከ300 በላይ ምእመናን የተመለከቱት ሲሆን ከተሰበሰበውን አስተያየት የብዙኃኑን ስሜት የነካ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል። ዓውደ ርእዩን የተመለከቱ ምእመናን በዕለቱ ቀረበው ከነበሩት ፕሮጀክቶችን መካከል እየመረጡ የወሰዱ ሲሆን በኦንላይን በተዘጋጀው የልገሳ ድረ ገጽ (http://www.gedamat.org) ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል መልእክት በዲ/ ተገኔ ተክሉ የቀረበ ሲሆን በመክፈቻው ላይ በተገኙ ካህናትና ተጋባዥ እንግዶች የተለያየ አስተያየት ተሰጥቷል።
ለሁለት ቀን ክፍት ሆኖ የቆየውን ዐውደ ርዕይ ከ300 በላይ ምእመናን የተመለከቱት ሲሆን ከተሰበሰበውን አስተያየት የብዙኃኑን ስሜት የነካ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል። ዓውደ ርእዩን የተመለከቱ ምእመናን በዕለቱ ቀረበው ከነበሩት ፕሮጀክቶችን መካከል እየመረጡ የወሰዱ ሲሆን በኦንላይን በተዘጋጀው የልገሳ ድረ ገጽ (http://www.gedamat.org) ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በዚህ ክፍል ስለ አብነት ት/ቤት ከስሙ ትርጓሜ ጀምሮ፣ አብነት ት/ቤት ምን ማለት እንደሆነ፣ ምን አይነት ትምህርት በውስጡ እንደሚያጠቃልል፣ እንዴት እንደተጀመረ፣ በኢትዮጵያ ስለነበሩ እና ስላሉ የአብነት ት/ ቤቶች ያሳየ ክፍል ነው።
አብነት ማለት አባትነት ማለት ሲሆን በአብነት ትምህርት ውስጥ መምህሩ በእውቀት አርአያነት፥ ተማሪው ደግሞ በትህትና አርአያነት ልክ እንደ አባት መምህሩ ለትውልዱ ተማሪው ደግሞ ለጓደኞቹ እና በአካባቢው ለሚኖረው ማኅበረሰብ በህይወቱ በማስተማር አብነት እንደሚሆን ተገልጿል።
የአብነት ትምህርት ጀማሪው እግዚአብሔር አዳምን በቃል በማስረዳት እንደጀመረው፣ ከዛም በሙሴ በጽሁፍ እንደተጠናከረ፣ በመቀጠልም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባር እንዳጸናው ተገልጿል።
ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶችም በትእይንቱ ላይ ሰፊ ሽፋን ያገኙ ሲሆን፥ መቼ እንደተመሰረቱ፣ በአብነት ትምህርት ላይ የነበራቸው እና ያላቸው ፋይዳ በሰፊው ተገልጿል። እንዲሁም እነኝህ የአብነት ት/ቤቶች ያፈሯቸው ታላላቅ ሊቃውንት እንደ አለቃ አያሌው ታምሩ : አለቃ አካለወልድ እንዲሁም ከእነ ቅዱስ ያሬድ ጀምሮ እነማን እንዳስተማሩባቸው ተገልጿል።
2. የአብነት ት/ቤቶች የሥርዓተ ትምህርት አደረጃጀትበዚህ ክፍል የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት ምን አይነት ይዘት እንዳለው ተገልጿል። በገለጻውም መሰረት የአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጠው ራሳቸውን በቻሉ የትምህርት ዘርፎች (የጉባኤ ቤቶች)በተከፋፈለና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ መሆኑ ተገልጿል። የጉባኤ ቤቶች የሚባሉትም ንባብ ቤት ፣ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና መጻሕፍት ቤት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪ ባሕረ ሓሳብ (አቡሻሐር) እና አክሲማሮስ ራሳቸውን በቻሉ ጉባኤ ቤቶች ይሰጡ እንደነበር ተመልክቷል።
3. የአብነት ት/ቤቶች አስተዋጽኦ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር
የአብነት ት/ቤቶች ለቤተክርስቲያን ታላላቅ መምህራን እና ሊቃውንትን በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የተብራራ ሲሆን፣ ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መኩሪያ የነበሩ እነሎሬት ጸጋዮ ገብረ መድኅን እና ሃዲስ ዓለማየሁን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ሰዎችን እንዳፈሩ ተገልጿል።
በዚህ ክፍል ውስጥ የሼክስፒር ሶኔት የሚባለው በለ 14 መስመር የቅኔ ስልት ከቤተክርስቲያን የቅኔ ስልት ጋር በማነጻጸር የቤተክርስቲያን የቅኔ ስልት በተሻለ ሁኔታ ሃሳብን ለመግለጽና ለማመስጠር እንደሚያገለግል ተብራርቷል።
4. አኗኗር በአብነት ት/ቤት
በዚህ የትእይንት ክፍል ውስጥ፣ የአብነት ተማሪው ከቤቱ ከትምህርት ከወጣ በኋል ተምሮ አንድ ደረጃ እስኪደርስ አኗኗሩ ምን እንደሚመስል እና የሚያጋጥሙት ፈተናዎች ምን እንደሚመስሉ በስዕል፣ በድምጽ እና በቪዲዮ ቅንብር ተብራርቷል።
በተለይ ተማሪው ምግቡን ለማግኘት ከውሻ፣ ከተፈጥሮ እና ከበሽታ ጋር ምን ያህል ግብ ግብ እንደሚገጥም በአብነት ት/ቤት ሕይወት ባለፉ ሊቃውንት እና የአብነት ተማሪዎች የቪዲዮ ምስክርነት የተገለጸበት ሁኔታ ልብን የሚነካ ነበር።
5. የአብነት ት/ቤቶች ያጋጠሙአቸው ዋና ዋና ችግሮች እና መንስኤዎቻቸው
በዚህ ክፍል ውስጥ፣ እነኝህ ለቤተክርስቲያን እና ለሃገር ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሊቃውንት መፍለቂያ የሆኑ የአብነት ት/ቤቶች በአሁኑ ሰዓት የተጋረጠባቸውን ፈተናዎች በተጠኑ መረጃዎች፣ በፎቶግራፍ እና በቪዲዮ በተደገፈ ሁኔታ ለታዳሚው የቀረበ ሲሆን፣ የተማሪውን እና የመምህራኑን ቸግር የሚያሳዮ ቪዲዮዎች ሲቀርቡ በትዕይንቱ ላይ የተገኙ አንዳንድ ምእመናን ሃዘናቸውን መቆጣጠር ተስኖአቸው ሲያለቅሱ ታይተዋል።
በዚህ ክፍል ውስጥ መፍትሄ እንዲሰጥ ሊረዳ ይችላል በሚል የችግሮቹ መንስኤዎች በሰፊው ተብራርተዋል። ከመንስኤዎቹም ውስጥ የምእመናን አቅም ማነስ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት የአብነት ትምህርቱን አስተዋጽኦ ያለማገናዘብ ተጠቅሰዋል።
6. የአብነት ትምህርት ቤቶች ነገ
አሁን በአብነት ት/ቤቶች ላይ ያጋጠመው ችግር እንዳለ ከቀጠለ በቤተ ክርስቲያን እና በሃገር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን እንደሆነ በዚህ ክፍል የተብራራ ሲሆን፣ በችግሩ ምክንያት ከፊታችን የተጋረጠውን አደጋ እንዳይከሰት ለመከላከል በዚህ የትዕይንት ክፍል ውስጥ የመፍትሔ ሃሳብ ይሆናሉ የተባሉ ሃሳቦች ተጠቁመዋል። መፍትሄዎቹም ተማሪዎቹን በተመለከተ፣ መምህራኑን በተመለከተ፣ ገዳማቱ እና አድባራቱን፣ የመማሪያ ቁሳቁስን በተመለከተ በሚል እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱን በተመለከተ በዝርዝር ቀርበዋል።
7. ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት ት/ቤቶች ያደረገው እና እያደረገ ያለው አስተዋእጽዎ
በዚህ ክፍል ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ለምን ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ፣ አሁን እየተሰሩ እና የታቀዱ ስራዎች፣ የታዩ ውጤቶች እና ከእኛ ምን ይጠበቃል? በሚል ሰፊ ገለጻ የተሰጠ ሲሆን አያይዞም ማኅበሩ እየሰጠ ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎት በመደገፍ በማጠናከርና ከማኅበሩ ጎን በመሆን ሁሉም ክርስቲያን የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ያስገነዘበ ነበር::
በዚህ ክፍል ውስጥም በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ገዳማትን በቀላሉ በአንድ ጊዜ ስጦታ ወይንም በየወሩ በሚቆረጥ ስጦታ ለመርዳት የሚያስችለው ድረ ገጽhttp://www.gedamat.org ተዋውቋል።
ባጠቃላይ “በእንተ ስማ ለማርያም” በሚል የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት የአብነት ትምህርት ቤቶች በቀጣይና ዘመኑን በዋጀ መንገድ ሊቀጥሉ የሚችሉበትን ስልት መቀየስና አስፈላጊ መሆኑን ያመላከተና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመሆን በስፋት መሥራት እንደሚገባ ያመላከተ ነበር ::